የቢሮው ገፅታ

የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ሴክተር ባለፉት ሦስት ዙር የስትራቴጂክ ዕቅድ ትግበራ ዓመታት እና በመጀመሪያው ዙር የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓመት በክልሉ ፈጣንና ቀጣይነት ያለውን ልማት ለማረጋገጥ፣ ድህነትን ለመቀነስ የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል፣ በተለይም በከተሞች አካባቢ ስር ሰዶ የቆየውን ሥራ አጥነት ለማስወገድ ራዕይ ሰንቆ፣ ተልዕኮውን በግልጽ አስቀምጦ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ከክልሉ ስትራቴጂዎች ጋር የሚጣጣሙ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ፣ የኢንዱስትሪና የንግድ ሪፎረሞች ነድፎ አገልግሎቶችን በማስፋፋት  ለኢኮኖሚው የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሴክተር በቀድሞው ንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ሴክተር እና በግብይትና ህብረት ሥራ ሴክተር የተለያዩ የአደረጃጀትና የአወቃቀር ሂደቶችን ያለፈ ተቋም ነው፡፡ በተሻሻለው የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግስት የአስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 161/2008 ዓ/ም መሠረት ተጠሪነታቸው ለቢሮ የሆኑ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ መረጃ አገልግሎት፣ የንግድ ኢንስፔክሽንና ሬጉሌሽን፣ የሸማቾች ጥበቃና ድጋፍ ፣ የገበያ ልማትና ግብይት አስተዳደር፣ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ፣ የግብርና ምርት ግብይት ዋና የሥራ ሂደቶችና ደጋፊ የስራ ሂደቶችን በአደረጃጀት ያቀፈ ነው፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በሴክተሩ ሥር የሚገኙ ከላይ የተገለጹት ተቋማት የሴክተሩን ልማት ለማፋጠን የአምስት አመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተዘጋጅቶና በክልሉ ካቢኔ ፀድቆ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የተገባ ሲሆን በግቦቹ ዙሪያ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫና ለፈጻሚዎች የክህሎት ክፍተት ማሟያ ስልጠናዎች እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡
በሴክተሩ ያለው ፓብሊክ ሰርቪስ የመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በጥልቀት አውቆና አምኖ የሴክተሩን ልማት ዕቅዶች ተፈጻሚ ለማድረግ እንዲችል በፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ግልጸኝነት ተፈጥሮ ተግባራዊ ሲደረጉ ከመቆየታቸውም በላይ የተገልጋዩችን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሠረታዊ የአሠራር ስርዓት ለውጥ /BPR/ ጥናት በሁሉም ዘርፍ ተካሂዶ ፣ አፈፃፀሙ በሙከራ ትግበራ ተገምግሞ ወደ ሙሉ ትግበራ እንዲሸጋገር ተደርጓል፡፡
በሴክተሩ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማሳለጥና ፈፃሚ አካል የሚመራባቸውን የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች፣ አዋጆች፣ ደንቦች፣ የአፈጻጸም መመሪያዎች እና የትግበራ ማኑዋሎች ተዘጋጅተው ክልላችን በርካታ የቱሪዝም መስህቦች፣ ታሪካዊ ቅርሶች፣ ፓርኮች፣ ጥብቅ የአደን ቦታዎች እንዲሁም በዩኔስኮ የአለም ቅርስነት የተመዘገቡትን የታችኛው ኦሞ ሸለቆ ፓሊዩንቶሎጂ የቅድመ ታሪክ ቦታዎችን፣ ትክል ድንጋዩች ባለቤት በመሆኑ በከፍተኛ ደረጃ ሊያድግ የሚችል የቱሪዝም ገበያ ዕድል አለው፡፡
የክልሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በአብዛኛው የተመሰረተው በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ እንደመሆኑ መጠን በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ከሚከሰቱ መጠነኛ ችግሮች በስተቀር ኢኮኖሚው በተረጋጋ ሁኔታ እያደገ የመጣበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ባለፉት ዓመታት በክልሉ እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ተከስቶ ከነበረው የዋጋ ግሸበት አንጻር ሲታይ በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች የሚያረጋግጡ ከመሆኑም ባሻገር ወደ ኢንዱስትሪ ሴክተር ያለው ሽግግር ጤናማ መሆኑን በግልጽ ያመለክታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የክልሉ ሕዝብ የነፍስ ወከፍ ገቢ መጨመር፣  የመግዛት አቅሙ ማደጉንና የኑሮ ደረጃው የዚያኑ ያህል እየተሻሻለ መምጣቱን መረዳት ይቻላል፡፡
የክልሉን ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ያረጋገጠ አመቺና አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ የኅብረተሰቡን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማስጠበቅ ልማትና ዕድገትን ማምጣትና ሰላምን ማረጋገጥ በሚያስችል ሁኔታ መንግስታዊ መዋቅሩ የሕግ አውጪ፣ አስፈጻሚና የዳኝነት አካላትን በመለየት ከክልል እስከ ቀበሌ አስተዳደር ድረስ ተደራጆቶ ሥራውን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በዚሁ መሠረት ክልሉ በ14 ዞኖች ፣ በ4 ልዩ ወረዳዎች፣ በ136 ወረዳዎች፣ በ28 የከተማ አስተዳደሮች፣ በ3,631 የገጠርና በ341 የከተማ ቀበሌያት ተደራጅቷል፡፡ የክልሉ መንግስት ለኅብረተሰቡ ተገቢውንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ አሳታፊ የሆነ አሰራር ለማስፈንና የሕዝቡንም የሥልጣን ባለቤትነትና የሀብት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ያልተማከለ አሰራርን በመዘርጋት በጀት፣ ሥልጣንና የሰው ኃይል ወደ ወረዳ በማውረድና ወረዳን ማዕከል በማድረግ እየተከናወነ ያለው እንቅስቃሴ ለዴሞክራሲ ሥርዓት እውን መሆን ማረጋገጫ ነው፡፡